ማርካን ትሬዲንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ከአዲስ-ሞጆ-መቂ ድረስ የሚዘልቀውን የ131 ኪሎ ሜትር መንገድ ከባድ የጥገና ሥራ ለመገንባት አሸናፊ ሆነ።

በየዓመቱ ቢሊዮኖች ዋጋ ያላቸው የመንገድ ግንባታ የኮንትራት ስምምነቶች የሚፈፀምበት የቀድሞ አውራ ጐዳና የአሁኑ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ዋና መሥሪያ ቤት ሕንፃ ጠባብ አዳራሽ ባለፈው ሐሙስ ከወትሮ በተለየ ተጨናንቋል፡፡

በዚህች ጠባብ አዳራሽ በተለይ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በአንድ ቀን የሚደረጉ የኮንትራት ስምምነቶች ከሦስት ወይም ከአራት አይበልጡም ነበር፡፡ በሐሙሱ የመንገድ ግንባታ የኮንትራት ስምምነቶች ግን በአንድ ጊዜ 5.6 ቢሊዮን ብር ዋጋ ያላቸው ሰባት የመንገድ ፕሮጀክቶች ኮንትራቶች ተፈርመዋል፡፡

የዕለቱን ኮንትራት ስምምነቶች የተለየ ያደረገው ዋነኛ ክስተት ደግሞ ሰባቱንም የመንገድ ፕሮጀክቶች ጨረታ ያሸነፉትና ግንባታውን ለማካሄድ ከባለሥልጣኑ ጋር ኮንትራት የተፈራረሙት የአገር በቀል ኮንትራክተሮች መሆናቸው ነው፡፡ ከዚህ ቀደም በተከታታይ የሚፈረሙ ኮንትራክተሮች የውጭ ኮንትራክተሮች የሚካተቱበት የነበረና በሰባት ተከታታይ ጨረታዎች አገር በቀል ኮንትራክተሮች አሸናፊ ሆነው ስለማያውቁ የዕለቱን የግንባታ ስምምነቶች የተለየ እንደሚያደርገው ተገልጿል፡፡

የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ አርዓያ ግርማይም ፕሮጀክቶች ያሸነፉት የአገር በቀል ድርጅቶች መሆናቸው መልካም አጋጣሚ መሆኑን ገልጸው፣ ይህም ባለፉት 21 ዓመታት መንግሥት በመንገድ ዘርፍ ልማት ፕሮግራሙ ለአገር በቀል የሥራ ተቋራጮችና ለባለሙያዎቻቸው በፈጠረው ዕድል ነው ብለዋል፡፡ በተከታታይነት በሰጠው የአቅም ግንባታ ፕሮግራም እንዲሁም የዕውቀትና የክህሎት ሽግግር ፕሮግራሞች ውጤታማነት ማሳያ ተደርጎ ሊወሰድ እንደሚችልም ጠቅሰዋል፡፡ የአገር ውስጥ የሥራ ተቋራጮቻችን በዓለም አቀፍ ደረጃ አንቱ የተባሉ ድርጅቶችን ማሸነፍ መጀመራቸው አገራዊው የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ የማስፈጸም አቅም አድጎና የአገር ውስጥ የገበያ ፍላጎትን አሟልቶ በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ ሆኖ ለማየት የተያዘውን ዕቅድ ለማሳካት በር የከፈተ ስለመሆኑም ገልጸዋል፡፡  

በአጠቃላይ አገር በቀል ኮንትራክተሮች ነግሰውበታል በተባለው የሐሙሱ የሰባት መንገድ ሥራ ፕሮጀክቶች የኮንትራት ስምምነቶች ውስጥ አንዱን የመንገድ ሥራ ፕሮጀክቶች ለመገንባት አሸናፊ የሆነው ደግሞ ማርካን ትሬዲንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ነው። ማርካን ከባለሥልጣኑ የተረከበው የመጀመሪያው ሥራ ከአዲስ-ሞጆ-መቂ ድረስ የሚዘልቀውን 131 ኪሎ ሜትር መንገድ ከባድ የጥገና ሥራ ነው፡፡ማርካን ይህንን ከባድ የጥገና ሥራ ለማከናወን የጨረታ አሸናፊ የሆነበት ዋጋ 210.31 ሚሊዮን ብር ነው፡፡ ማርካንን ወክለው የኮንስትራት ስምምነቱን የፈረሙት የማርካን ሥራ አስኪያጁ አቶ ተስፋዬ ግዛው፣ ይህ ዕድል ለኩባንያቸው ትልቅ ጠቀሜታ ያለው መሆኑ ገልጸዋል፡፡

እስካሁን ሰብ ኮንትራት ሥራዎችን ሲሠሩ መቆየታቸውን የገለጹት አቶ ተስፋዬ፣ አሁን አሸናፊ የሆኑበትን ሥራ በተያዘለት የጊዜ ገደብ ለማጠናቀቅ ቃል ገብተዋል፡፡  ለባለሥልጣኑ ሥራ የመጀመሪያ የሆነው ዮናታን አብይ ጠቅላላ ሥራ የተባለው ድርጅት አሸናፊ የሆነው የመቂ ሻሸመኔ-ሐዋሳ ድረስ ያለውን 146 ኪሎ ሜትር መንገድ ነው፡፡ መንገዱን 197.1 ሚሊዮን ብር ለመገንባት ውል ፈጽሟል፡፡ በዕለቱ የኮንትራት ውል የፈጸሙት ኮንትራክተሮች የተረከቡትን ሥራ በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ ለማጠናቀቅ ቃል ገብተዋል፡፡